NEW YEAR 2016

የሰላም ጥሪ በአዲስ ዓመት

ውድ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ፳፻፲፮ አዲሱ ዓመት አደረሳችሁ። መልካም የዘመን መለወጫ በዓል ይሆንላችሁ ዘንድ ከልብ እየተመኘን በአዲስ ዓመት መንፈስ ዲፌንድ ኢትዮጵያ ለመንግስት እና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ጦር አንግበው ለሚዋጉ ወገኖች የሚከተለውን የሰላም ጥሪ ያቀርባል።

 

አሮጌውን ዓመት ተሰናብተን አዲሱን ዓመት ስንቀበል ሁላችንም በሀገራችን ሰላምን ለማስፈን የየበኩላችንን ጥረት ማድረግ እንዳለብን በመገንዘብ ሊሆን ይገባል። የአዲሱን ዓመት ምእራፍ ስንከፍት በ፳፻፲፭ በተለያየ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡትን፣ አካላቸው የጎድለ፣ ለእስር የተዳረጉ እንዲሁም ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ወገኖቻችንን በማሰብ፤ በሀገራችን ሰላም ሰፍኖ፣ ልዩነቶቻችንን በውይይት እየፈታን እና እየተሳሰብን፤ ወገኖቻችንን ከችግር ለማውጣት የምንሰራበት ዓመት ይሆን ዘንድ በመመኘት ነው።

 

አላግባብ የፈሰሰው ደም አልደረቀ ይሆናል፤ የቅርብ ታሪካችን የማይድን የሚመስል ቁስልን ትቶ አልፎ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ቁጭ ብለን ካልተነጋገርን፣ ይቅር ካልተባባልን እና ልዩነቶቻችንን በውይይት ካልፈታን ሌላ አዲስ ቁስል፣ ሌላ አዲስ ደም እየፈሰሰ ማለቂያው ወደማያምር የመተላለቅ መንገድ እንጓዛለን ሀገራችንንም እናደቃለን።

 

አዲሱ መት አዲስ አስተሳሰብን ካላመጣ ከአሮጌው በምን ሊለይ ይችላል? ከእልህ እና ከበቀል መንፈስ ወተን ሰላምን ካላመጣን ነገን ለመኖራችን እና የሀገራችንን አንድነት ለማስጠበቃችን ምን ዋስትናስ አለን?

 

የአባቶቻችንን የጀግንነት ታሪክ እና ለአፍሪካ ነጻነት ያበረከቱትን አስትዋጽዎ እያወራን እኛ ሰላምን ለማምጣት እና የራሳችንን ወገን ህይወት ለማዳን ካልሰራን ምኑን ታሪክን አስቀጠልን? እነሱ የገነቡትን እኛ አፈረስን እንጂ።

 

ስለዚህም ዲፌንድ ኢትዮጵያ የሚከተሉትን የሰላም ጥሪ ያቀርባል፦

 

፩.    አፋጣኝ የተኩስ ማቆም ስምምነት በሁሉም አካላት ይደረግ ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።

፪.    ሁሉም ወገኖች የዜጎችን መሰረታዊ መብት እንዲያከብሩ ጥሪ እናቀርባለን።

፫.    መንግስት ሁሉን አካታች የሰላም ውይይት በአስቸኳይ እንዲያስጀምር ጥሪ እናቀርባለን።

፬. የይቅር መባባል እና ዘላቂነት ያለው ሰላምን የማምጣት ስራ በሀይማኖት አባቶች እና አዛውንቶች መሪነት ይጀመር ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።

፭. ከሚኖሩበት አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን የማስመለስ እና ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራ በአስቸኳይ ይሰራ ዘንድ ጥሪ እናቀርባለን።

፮. በውጭ ሀገራት የምንገኝ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሰላም ወደ ሀገራችን የሚመለስበትን ቀን ለማቅረብ ጠንክረን እንድንሰራ ጥሪ እናቀርባለን።

 

 

የጦርነትን አስከፊነት ሁላችንም አይተነዋልና በቃን ልንል ይገባል። ከትናንት እንማር! ከእርስ በእርስ ጦርነት ተሸናፊ እንጂ አሽናፊ የለውም። ዲፌንድ ኢትዮጵያ ሰላምን በሀገራችን ለማምጣት የበኩላችንን ጥረት እንደምናደርግ ቃል እንገባለን።

 

 

መልካም አዲስ ዓመት።

ዲፌንድ ኢትዮጵያ

ለንደን

ዩናይትድ ኪንግደም

ጷግሜ ቀን ፳፻፲፭ ዓ..

info@defendethiopia.com

www.defendethiopia.com